የኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በድግሪና በተለያዩ የብቃት ደረጃዎች ያሰለጠናቸውን ከ850 በላይ ሰልጣኞችን አስመረቀ
የኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በኮሮና ምክንያት ተቀቋርጦ የነበረውን ስልጠና በማካካስ ከብቃት ደረጃ I እስከ ደረጃ IV ባሉ የተለያዩ የሙያ መስኮችና በድግሪ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን ሰልጣኞች የካቲት 20 ቀን 2013 አስመረቀ፡፡ ኮሌጁ ከደረጃ I እስከ ደረጃ IV ያሰለጠናቸውን ሰልጣኞች (ወ 426፤ ሴ፤ 295፤ ድ– 721) ለ14ኛ ጊዜ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ፤ በአውቶሞቲቭና በኤሌክትሲቲ/ኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ በድግሪ ፕሮግራም (ወ- ሴ– 14 ድ-136) ለ2ኛ ጊዜ በአጠቃላይ 857 ሰልጣኞች አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስርዐቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ዲን አቶ መላኩ አራጋው ኮሌጁ ከተመሰረተበት 1994 ጀምሮ ላለፉት 19 ዓመታት ከአስራ አራት ሺህ ስምንት መቶ በላይ ሰልጣኞችን በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ በቅጥርም ይሁን በመደራጀትና በግል ሥራ ፈጠራ ወደ ሥራ ተሰማርተዋል ብለዋል፡፡ ማስመረቅ የኮሌጁ የመጨረሻ ግብ አይደለም ያሉት የኮሌጁ ዲን ሁሉም ምሩቃን በሀገር ደረጃ አስከ 90 ፐርሰንት የሚሆኑት ተመራቂዎች በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የሥራ ባለቤት እንዲሆኑ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንሠራለን ብለዋል፡፡ ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍና ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመገንባት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ሴክተር ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት መጣሉን ገልጸው ይኽንም ኃላፊነት ለመወጣት ኮሌጁ ቆርጦ በመነሳት ኢኮኖሚው የሚፈጥራቸውን ኢንዱስትሪዎች ሊሸከም የሚችል በሙያ ክህሎቱና ብቃቱ የተረጋገጠ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል የፊናውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡