በኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የፕሮጀክት ግንባታ ማሰጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
Posted 2021-06-12 00:53:38
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በአምስት ዓመታት ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደስራ የሚገቡ ሰባት የምስራቅ አፍሪካ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ማሰልጠኛ የልህቀት ማእከላትን ከ150 ሚሊየን ዶላር በላይ መድቦ በተለያዩ አካባቢዎች እያስገነባና እያጠናከረ ይገኛል፡፡ ከግንባታዎቹ መካከል አንዱ የሆነው የኮምቦልቻ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ልህቀት ማእከል የመሰረት ድንጋይ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ሚንስትር ክቡር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ሰኔ 02/2013 ዓ/ም የተቀመጠ ሲሆን ግንባታዉ በ12.85 ሚሊየን ዶላር ይካሄዳል፡፡ የኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ የስልጠና ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያስችለውን የፕሮጀክት ግንባታ የማሰጀመሪያ መርሀ ግብር ከፍተኛ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ መስተዳድር የመንግስት ባለስልጣኖች በተገኙበት አካሂዷል። የኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መላኩ አራጋዉ የልህቀት ማእከላቱ መገንባት የትምህርት ግብአትን በሟሟላት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና በገበያ ተፈላጊ የሆነ የሰው ሃይል ለማሰልጠን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡